ኢየሱስ አምላክ ነኝ ብሏልን?

አማርኛ · srpski · Polski · Français · Русский · Deutsch · Italiano · Română · English

ሙስሊሞች ኢየሱስ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከአላህ ባሪያዎች አንዱ እና ከተከበሩ መልእክተኞቹ ውስጥ አንዱ መሆናቸውን ያምናሉ። አላህ ኢየሱስን ወደእስራኤል ልጆች በአላህ ብቻ እንዲያምኑ እና እርሱን ብቻ እንዲገዙ ይጣሩ ዘንድ ልኳቸዋል።

አላህ ኢየሱስን (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እውነት ይናገሩ እንደነበር በሚያረጋግጡ ተአምራት ደግፏቸዋል። ኢየሱስ ከድንግል ማርያም (መርየም) ያለ አባት ነበር የተወለዱት። አይሁዶች ተከልክለው ከነበሯቸው ነገሮች ውስጥ የተወሰኑትን ፈቅደዋል፤ አልሞቱም፤ ጠላቶቻቸው አይሁዶችም አልገደሏቸውም፤ ይልቁንም አላህ ከእነሱ በማዳን ወደ ሰማየ ሰማያት በህይወት እንዲያርጉ አድርጓቸዋል። ኢየሱስ ተከታዮቻቸውን ስለ ነብያችን ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መምጣት ነግረዋቸዋል። ኢየሱስ በዓለም ፍፃሜ መዳረሻ ተመልሰው ይመጣሉ። በትንሣኤ ቀን አምላክ ስለመሆናቸው ይነገር የነበረውን ነገር ሁሉ ራሳቸው ያስተባብላሉ።

በትንሳኤ ቀን፥ ኢየሱስ ከዓለማቱ ጌታ ፊት ይቆማሉ፤ እርሱም የእስራኤል ልጆችን ምን እንዳሏቸው በምስክሮቹ ፊት ይጠይቃቸዋል፤ አላህ እንደሚለው፡-

አላህም፡- «የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብላሃልን» በሚለው ጊዜ (አስታውስ)። «ጥራት ይገባህ፤ ለእኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም። ብዬው እንደሆነም በእርግጥ አውቀኸዋል። በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ። ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም። አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና» ይላል። «በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ ማለትን እንጂ ለነርሱ ሌላ አላልኩም። በውስጣቸውም እስካለሁ ድረስ በእነርሱ ላይ ተጣባበቂ ነበርኩ። በተሞላኸኝም ጊዜ (ባነሳኸኝ ጊዜ) አንተ በእነሱ ላይ ተጠባባቂ ነበርክ። አንተም በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ ነህ። ብትቀጣቸው እነርሱ ባሮችህ ናቸው። ለእነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ» (ይላል)።

ቁራኣን - 5:116-118
(ፍቹ ሲተረጎም)

እውነተኛ ምርመራ እንደሚያሳየው ኢየሱስ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ግልፅ በሆነና በማያሻማ መንገድ ፈፅሞ አምላክ ነኝ ብለው አያውቁም። አምላክ ናቸው ብለው ያሉትና ይህንን የናኙት አንዳቸውም ከኢየሱስ ጋር በአካል ተገናኝተው የማያውቁት የሐዲስ ኪዳን ወንጌል ፀሃፊያን ነበሩ። ትክክለኛዎቹ የኢየሱስ ሐዋርያት ይህን ስለማለታቸውም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ስለመፃፋቸው ምንም ማስረጃ የለም። ይልቁንም ኢየሱስ በቋሚነት አምላክን ብቻ ሲገዝዛ እና ሌሎችንም እሱን ብቻ ወደማምለክ ሲጣራ ይታይ ነበር።

ኢየሱስ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ጌታ ናቸው የሚለው ብይን ለኢየሱስ ሊሰጥ አይችልም፤ ብይኑ ከአምላክ ውጪ ሌሎችን ነገሮች አማልክት አለማድረግን እና በሰማይም ሆነ በመሬት ያለን ማንኛውም ነገር በጣዖትነት አለመውሰድን ከሚደነግገው የመጀመርያው ትእዛዝ ጋር ፍፁም የሚጋጭ እስከሆነ ድረስ። በተጨማሪም፥ አምላክ ራሱ የፈጠረው ፍጡር መልሶ አምላክ ሆነ ቢባል ከምክንያታዊነት አንፃር ወልጣቀኝ ነው የሚሆነው።

በመሆኑም፥ የእስልምና ብይን ብቻ ነው ተቀባይነት ያለውና ከቀደሞ የራዕይ መልዕክት ጋር በወጥነት የሚጣጣም የሚሆነው፤ ኢየሱስ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ነብይ እንጂ አምላክ አልነበሩም።

ምንጭ: seekersguidance.org · islamqa.info · islamweb.net · islamqa.info
ትርጉም በ: Abdu Ahmed