እስልምና ስለ ቂያማ (ፍርድ) ቀን ምን ይላል?
እንደ ክርስቲያኖች ሁሉ ሙስሊሞችም የአሁኑ አለም ህይወት ለቀጣዩ አለም የህላዌ አድማስ የሙከራ ዝግጅት ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ይህ ሕይወት እያንዳንዱን ግለሰብ ከሞት በኋላ ለሚጠብቀው ሕይወት መፈተኛ ነው። መላው አጽናፈ ዓለም የሚጠፋበት እና ሙታን ለፍርድ የሚነሡበት ቀን ይመጣል። ይህ ዕለት የማያልቅ ህይወት የሚጀመርበት ቀን ይሆናል። ይህም ቀን የትንሳዔ ቀን ነው። በዚያም ዕለት ሰዎች ሁሉ እንደ እምነታቸውና እንደየሥራቸው ከአሏህ ዘንድ ምንዳቸውን ያገኛሉ። እነዚያ “ከአሏህ በቀር እውነተኛ አምላክ የለም፤ ሙሐመድም የአሏህ መልእክተኛ (ነብይ) ናቸው” የሚለውን አምነው የሞቱ እና ሙስሊም የሆኑ ሰዎች በዚያ ቀን ምንዳቸውን በማግኘት ዘላለማዊ ጀነትን እንዲገቡ ይደረጋሉ፤ ልክ አሏህ እንዳለው፡-
እነዚያም ያመኑት በጎ ሥራዎችንም የሠሩት እነዚያ የገነት ጓዶች ናቸው። እነርሱ በውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ናቸው።
ቁራኣን - 2:82(ፍቹ ሲተረጎም)
ነገር ግን እነዚያ “ከአሏህ በቀር እውነተኛ አምላክ የለም፥ ሙሐመድም የአሏህ መልእክተኛ (ነብይ) ናቸው” በሚለው ሳያምኑ የሞቱ ወይም ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ጀነትን ለዘላለም አጥተው ወደ ጀሀነም እሳት ይወርዳሉ፤ አሏህ እንደተናገረው፡-
ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም። እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው።
ቁራኣን - 3:85(ፍቹ ሲተረጎም)
እርሱም እንደተናገረው፡-
እነዚያ የካዱና እነርሱም በክህደታቸው ላይ እንዳሉ የሞቱ ከእነሱ ከአንዳቸው በምድር ሙሉ የሆነ ወርቅ (ቢኖረውና) በርሱ ቢበዥበትም እንኳ ፈጽሞ ተቀባይን አያገኝም። እነዚያ ለእነርሱ የሚያሰቃይ ቅጣት አላቸው። ለነርሱም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።
ቁራኣን - 3:91(ፍቹ ሲተረጎም)
አንድ ሰው ይህን ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፥ 'እስልምና ጥሩ ሐይማኖት እንደሆነ አስባለሁ፤ ግን ደግሞ እስልምናን ብቀበል ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼ እና ሌሎች ሰዎች ያሳድዱኝ እና ያፌዙብኝ ነበር። ታዲያ እስልምናን ካልተቀበልኩ ጀነት እገባና ከጀሀነም እጠበቅ ይሆን?'
መልሱ በቀደመው አንቀጽ አሏህ፥ “ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም። እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው።” ብሎ ያለው ነው።
ሰዎችን ወደ እስልምና እንዲጠሩ ነቢዩ ሙሐመድን ﷺ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከላከ በኋላ፥ አሏህ ከእስልምና ውጪ የትኛውንም ሌላ ሃይማኖት አይቀበልም። አሏህ ፈጣሪያችንና ረዳታችን ነው። በምድር ያለውን ሁሉ ለእኛ ፈጥሮልናል። እኛ ያሉን በረከቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ናቸው። ስለዚህ፥ ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ አንድ ሰው በአሏህ፣ በነብዩ ሙሐመድ ﷺ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወይም በሀይማኖቱ በእስልምና ማመንን ሲተው፥ በወዲያኛው ዓለም የሚጠብቀው ነገር ቅጣት ብቻ ነው የሚሆነው። በመሰረቱ፥ የተፈጠርንበት ዋና ዓላማ አሏህን በብቸኝነት ለማምለክ እና እርሱን ለመታዘዝ ነው፤ ልክ አላህ በቅዱስ ቁርዓን (51፡56) እንደተናገረው።
ዛሬ የምንኖረው ይህ ህይወት በጣም አጭር ነው። በመጨረሻው የፍርድ ቀን ከሃዲያን ምድር ላይ ያሳለፉት ህይወት አንድ ሙሉ ወይም ግማሽ ቀን ብቻ እንደነበር ያስባሉ፤ አሏህ እንዳለው፥
«በምድር ውስጥ ከዓመታት ቁጥር ስንትን ቆያችሁ» ይላቸዋል። «አንድ ቀንን ወይም ከፊል ቀንን ቆየን» ይላሉ . . .
ቁራኣን - 23:112-113(ፍቹ ሲተረጎም)
እርሱም እንዲህ ብሏል፥
የፈጠርናችሁ ለከንቱ መሆኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መሆናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?) የእውነቱም ንጉስ አላህ ከፍተኛነት ተገባው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም . . .
ቁራኣን - 23:115-116(ፍቹ ሲተረጎም)
ከሞት በኋላ ያለው ሕይወት (አኼራ) በጣም እውነተኛ ሕይወት ነው። መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊም ጭምር ነው። እዚያም የምንኖረው ከነፍሳችንና ከአካላችን ጋር ነው።
ይህን ዓለም ከአኼራ ጋር በማወዳደር፥ ነብዩ ሙሃመድ ﷺ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፥
የቅርቢቱ ዓለም ዋጋ ከመጨረሻው ዓለም ጋር ሲነፃፀር ኢምንትነቱ ጣትህን ባሕር ውስጥ ነክረህ የምታወጣት የውሃ ጠብታ ለባሕሩ ያላትን ዋጋ ያህል ነው።
Sahih Muslim, 2858
ትርጉሙም ምንድን ነው፥ የዚህ ዓለም ዋጋ ከአኼራ ጋር ሲወዳደር ጥቂት ጠብታ ውሃ ከባህር ጋር ሲወዳደር ያለውን አይነት ነው።
ምንጭ:
islam-guide.com
ትርጉም በ:
Abdu Ahmed