Islam Answers » መልሶች » አማርኛ » ኢንሻአሏህ ማለት ምን ማለት ነው?

ኢንሻአሏህ ማለት ምን ማለት ነው?

"ኢንሻአሏህ" (አሏህ ከፈቀደ) የሚለው አገላለፅ፥ አንድ ሙስሊም ወደፊት ሊያደርገው የሚፈልገውን ነገር በአሏህ ፈቃድ ላይ እንዲመሰረት ማድረግ እንደማለት ነው።

"ኢንሻአሏህ" ማለት የእስልምና ስነ ምግባር አካል ነው። ሙስሊሙ ወደፊት ለመፈፀም የሚከጅለውን ተግባር በገለፀ ቁጥር "ኢንሻአሏህ" እንዲል ታዟል።

ለማንኛውም ነገር «እኔ ይህንን ነገ ሠሪ ነኝም» አትበል። «አላህ የሻ እንደሆነ (እሰራዋለሁ)» ብትል እንጂ። (...)

ቁራኣን - 18:23-24
(ፍቹ ሲተረጎም)

ግለሰቡ ከወደፊት ተግባሮቹ ጋር በተያያዘ ቃሉን አክሎ ሲናገር፥ ጉዳዮቹ ሊፈፀሙም ላይፈፀሙም ይችላሉ። ሆኖም ግን "ኢንሻአሏህ" ካለ፥ የመፈፀማቸው ነገር ይበልጥ ተስፋ ይጣልበታል።

የነቢዩ ሱለይማን (ጠቢቡ ሰሎሞን) ታሪክም ይህንኑ ፍች የሚጠቁም ነው።

ነብዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፤ "ሱለይማን (የዳውድ ልጅ) ‹ዛሬ ማታ ከሰባ ሚስቶቼ ጋር እተኛለሁ፤ እያንዳንዳቸውም ወደፊት በአሏህ መንገድ ላይ የሚጋደሉ ጀግና ፈረሰኞችን ይፀንሳሉ።› ሲሉ ጓዳቸው 'አላህ ቢሻ' አለ። ነገር ግን ሱለይማን ያንን ባለማለታቸው ከእነዚያ ሴቶች መካከል መፃጉዕ ልጅን ከወለደችው ከአንዷ ሴት በስተቀር አንዳቸውም አላረገዙም ነበር።" ነብዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አክለውም እንዲህ አሉ፥ "ነቢዩ ሱለይማን (አላህ ቢሻ) ቢሉ ኖሮ በአሏህ መንገድ ላይ ሊጋደሉ ይችሉ የነበሩ ልጆችን ይወልዱ ነበር።"

Sahih al-Bukhari, 3424

ይህ እንግዲህ አንድ ሰው "ኢንሻአሏህ" በሚል ጊዜ ምኞቱ እና ፍላጎቱ የመሟላቱ ነገር ይበልጥ እውን እንደሚሆን ማሳያ ነው፤ ይሁን እንጂ ነገሩ ሁሌም የግድ እንዲህ ላይሆን ይችላል። አሏህ የሻው ነገር እውን ይሆናል። እጦት ወይም አለመሳካት ስውር ምርቃት ሊሆንም እንደሚችል ልብ ሊባል ይገባል።

(. . .) አንዳች ነገርን እርሱ ለናንተ የበለጠ ሲሆን የምትጠሉት መሆናችሁ ተረጋገጠ። አንዳችንም ነገር እርሱ ለናንተ መጥፎ ሲሆን የምትወዱት መሆናችሁ ተረጋገጠ። አላህም (የሚሻላችሁን) ያውቃል ግን እናንተ አታውቁም።

ቁራኣን - 2:216
(ፍቹ ሲተረጎም)

ምንጭ: islamweb.net · islamweb.net
ትርጉም በ: Abdu Ahmed