Islam Answers » መልሶች » አማርኛ » እስልምና የአረቦች ብቻ ነው?

እስልምና የአረቦች ብቻ ነው?

ይህ ፍፁም ሐሰት መሆኑን ለማረጋገጥ እጅግ ፈጣኑ መንገድ፥ አለም ላይ ካሉ ሙስሊሞች ከ15% እስከ 20% የሚሆኑት ብቻ አረቦች መሆናቸውን መግለጽ ነው። ከአረብ ሙስሊሞች ይበልጥ ብዙ የህንድ ሙስሊሞች፣ ከህንድ ሙስሊሞች ይበልጥ በርካታ የኢንዶኔዥያ ሙስሊሞች አሉ! እስልምና የአረቦች ብቻ ሃይማኖት እንደሆነ ማመን በእስልምና ታሪክ መባቻ ላይ በሐይማኖቱ ጠላቶች የተሰራጨ አፈ ታሪክ ነው። ይህ የተሳሳተ ግምት፥ ምናልባትም አብዛኞቹ የመጀመሪያ ትውልድ ሙስሊሞች አረቦች በመሆናቸው፣ ቁርዓን በአረብኛ ቋንቋ በመውረዱ እና ነብዩ ሙሀመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አረብ መሆናቸውን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የእስልምና አስተምህሮቶችም ሆኑ የተስፋፎት ታሪኩ፥ ቀደምቶቹ ሙስሊሞች የእውነት መልእክታቸውን ለሁሉም ብሔሮች፣ ዘሮችና ህዝቦች ለማዳረስ ማንኛውንም ጥረት ማድረጋቸውን ያሳያሉ።

ከዚህ ባሻገር አረቦች ሁሉ ሙስሊሞች፥ ሙስሊሞች ሁሉ ደግሞ አረቦች አለመሆናቸው ግልፅ ሊሆን ይገባል። አንድ አረብ ሙስሊም፣ ክርስቲያን፣ ይሁዲ፣ እምነት የለሽ - አልያም የሌላ የትኛውም ሐይማኖት ወይም አስተሳሰብ አራማጅ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም፥ እንደ ቱርክ እና ኢራን (ፋርስ) ያሉ አንዳንድ ሰዎች "አረብ" አድርገው የሚቆጥሯቸው ብዙ አገሮች ከነጭራሹ "አረብ" አይደሉም። በነዚህ ሀገራት የሚኖሩ ህዝቦች በአፍ መፍቻነት ከአረብኛ ውጪ ሌሎች ቋንቋዎችን ይናገራሉ፤ ብሎም የተለየ የዘር ሐረግ አላቸው።

ከነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ተልዕኮ ጥንስስ ጀምሮ ተከታዮቻቸው የተውጣጡት ሰፊ የማንነት ስብጥር ካላቸው ግለሰቦች እንደነበር መገንዘብ ጠቃሚ ነው - አፍሪካዊው ባሪያ ቢላል፤ የቤዛንታይን ሮማዊው ሱሄይብ፤ ይሁዲው ራባይ ኢብን ሴይለም፤ እንዲሁም የፋርሱ ሰልማን ነበሩ። ሐይማኖታዊ እውነታ ዘላለማዊና የማይለዋወጥ እንዲሁም የሰው ዘር አንድ አለም አቀፋዊ ወንድማማችነት በመሆኑ፥ ለሰው ልጅ የወረዱት የሐያሉ አምላክ መመሪያዎች ሁሌም ወጥነታቸውን የጠበቁ፣ ግልጽ እና ሁለንተናዊ መሆናቸውን እስልምና ያስተምራል።

የእስልምና እውነታ፥ ዘር፣ ብሔር ወይም ቋንቋ ሳይለይ መላ የሰው ዘርን ተሃሳቢ ያደረገ ነው። እስልምና ለመላ የሰው ዘር የወረደ አለም አቀፍ መልዕክት መሆኑን ለማረጋገጥ፥ ከናይጄሪያ እስከ ቦስኒያ ብሎም ከማሌዥያ እስከ አፍጋኒስታን የተንሰራፋውን ሙስሊም አለም መመልከት በቂ ነው --- ከሁሉም ዘሮችና ብሔሮች የተውጣጡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አውሮፓውያን እና አሜሪካውያን ወደ እስልምና በመትመም ላይ ያሉበትን ሁኔታ ሳናነሳ።

ምንጭ: spubs.com
ትርጉም በ: Abdu Ahmed

ተመሳሳይ ጥያቄዎች